Loading...

የከይዘን የአሰልጠኞች ስልጠና በአዳማ ከተማ ተሰጠ

ከኦሮሚያ 24 የፖሊቴክኒክ ኮሌጆች የተውጣጡ 48 የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኞች እንዲሁም የቴክኖሎጅ ሽግግርና ኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን የሥራ ሂደት ባለቤቶች ስልጠናውን ከተከታተሉት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ 10 ከአዳማ ከተማ ለተውጣጡ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢተርፕራይዞች አንቀሳቃሾች እና ከኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ የመጡ 12 አመራሮችና ባለሙያዎች በስልጠናው ተሳትፈዋል፡፡ የከይዘን የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰዱት በዓዳማ ከተማ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ነው፡፡ ለአስር ተከታታይ ቀናት በተሰጠው ስልጠና ከንድፈ ሀሳብ በተጨማሪ ሠልጣኞች በ7 የከይዘን ልማት ቡድኖች ተደራጅተው ችግሮችን በመለየትና የመፍትሔ ሐሳብ በማፍለቅ ተግባራዊ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤባ ገርባ እንደተናገሩት ሰልጣኞች በንድፈ ሀሳብና በተግባር ያገኙትን እውቀት ወደ መጡባቸው ተቋማት ሲመለሱ ማሰልጠንና ተግባራዊ ለውጥ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ክትትልና ግምገማ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የኢንዱስትሪና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ በበኩላቸው ከይዘንን በኢንተርፕራይዞች ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ከሰልጣኞች ብዙ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከይዘን ኢንስቲትዩት የመሠረታዊ ልማትና አገልግሎቶች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አወል ካሳው በበኩላቸው ሰልጣኞች በስልጣና ወቅት ለነበራቸው ትጋትና በቡድን ሥራ ወቅት ያሳዩትን ተነሳሽነት አድንቀው በስልጠናው የተገኘው ዕውቀት ልምድና ክህሎት በየመጣችሁበት ተቋም ተግባራዊ እንዲደረግ ኢንስቲትዩቱ ተከታታይ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ቢሮዎችና የየቴክኒክና ሙያ ተቋማት አመራሮችም ልጆችን በመደገፍ እና ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫዎት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ስልጠናው ጥቅምት 24/2011 ዓ.ም በአዳማ ሲጠናቀቅ የኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ በሰልጠናው ተሳትፎ ላደረጉ ስልጣኞች የምስክር ወረቀት ሰጥቷል፡፡

By |2019-01-23T17:20:45+00:00January 23rd, 2019|ዜና|0 Comments

About the Author:

Leave A Comment